Fana: At a Speed of Life!

በ4 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የተጣለው እገዳ ተነሳ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአራት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ መነሳቱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታውቋል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣ በሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ እና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ላይ እገዳ መጣሉ ይታወሳል።

ኢሰመኮ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መግለጫ÷ ከባለስልጣኑና ከታገዱት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማድረግ ለጉዳዩ መፍትሔ ለማስገኘት ሲሠራ መቆየቱን ጠቅሷል፡፡

በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የሚተላለፉ እገዳዎች በሲቪል ምኅዳሩ እና በማኅበር የመደራጀት መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይፈጥሩ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስቧል።

በተጨማሪም ኢሰመኮ በድርጅቶቹ እገዳ ላይ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ምርመራ ያከናወነ ሲሆን÷የደረሰባቸውን ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ለሚመለከታቸው አካላት ማጋራቱን ነው የገለጸው፡፡

ኢሰመኮ ባደረገው ጥረትም በአራቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ከዛሬ የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ መነሳቱን አስታውቋል፡፡

በሒደቱ ተባባሪ ለነበሩት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እና ሌሎች የመንግሥት አካላት እንዲሁም ለአራቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምስጋና አቅርቧል፡፡

የሚከሰቱ ችግሮችን የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ እና ሀገራዊ ጥቅምን በማስቀደም በመቀራረብ እና በመወያየት የመፍታት ልምድ ሊጎለብት አንደሚገባም አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.