በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ተጠባቂው የማድሪድ ደርቢ ዛሬ ምሽት ይደረጋል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ይደረጋሉ።
በዕለቱ ተጠባቂ መርሃ ግብር የወቅቱ ሻምፒዮን ሪያል ማድሪድ የከተማ ተቀናቃኙ አትሌቲኮ ማድሪድን ምሽት 5 ሰዓት በሳንቲያጎ ቤርናባው ያስተናግዳል።
በመድረኩ በፈረንጆቹ 2014 እና 2016 የፍጻሜ ተፋላሚ የነበሩት ሁለቱ ክለቦች በምሽቱ ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
አትሌቲኮ ማድሪድ በቅርቡ በሁሉም ውድድሮች ጥሩ አቋም ላይ እንደመገኘቱ ለሎስ ብላንኮዎቹ በምሽቱ ጨዋታ ፈታኝ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በተመሳሳይ ምሽት 5 ሰዓት አርሰናል ወደ ኔዘርላንድስ አቅንቶ የኤርዲቪዜውን ክለብ ፒ ኤስ ቪ አይንድሆቨን ይገጥማል።
በሌላ የምሽቱ መርሃ ግብር የአምና የፍፃሜ ተፋላሚ የነበረው ቦሩሺያ ዶርትሙንድ ምሽት 5 ሰዓት ላይ በሜዳው ሲግናል ኤዱና ፓርክ የፈረንሳዩን ክለብ ሊልን ያስተናግዳል።
ከነዚህ ጨዋታዎች ቀደም ብሎ ምሽት 2 ሰዓት ከ45 አስቶን ቪላ ከሜዳው ውጭ ከቤልጂየሙ ክለብ ብሩዥ ጋር ይገናኛል።