Fana: At a Speed of Life!

በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ሊቨርፑል ከ ፒኤስጂ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ ምሽት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ቀጥለው ሲደረጉ ሊቨርፑልን ከፒኤስጂ የሚያገናኘው ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል፡፡

በአሰልጣኝ አርኔ ስሎት እየተመራ በቀጥታ 16ቱን የተቀላቀለው የእንግሊዙ ክለብ ሊቨርፑል ወደ ፓሪስ አቅንቶ ከፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ ጋር በፓርክ ደ ፕሪንስ ምሽት 5 ሰዓት ላይ የጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

የአንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን እየመራ የሚገኘው ሊቨርፑል በውድድር ዓመቱ ተጨማሪ ዋንጫ ለማሳካት የሚያደርገውን ጉዞ አጠናክሮ ለመቀጠል የዛሬውን ጨዋታ አሸንፎ ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡

ባለ ሜዳው ቡድን ፒኤስጂ በበኩሉ ክለቡ እና ደጋፊው ለዓመታት የሚመኙትን የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ለማሳካት እና እስከ መጨረሻው ለመጓዝ በዛሬው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በተመሳሳይ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ሁለቱ የጀርመን ክለቦች ባየር ሙኒክ እና ባየር ሊቨርኩሰን በአሊያንዝ አሬና ሲገናኙ የካታላኑ ክለብ ባርሴሎና ወደ ፖርቹጋል በማቅናት ከቤኔፊካ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

ከእነዚህ ጨዋታዎች ቀደም ብሎ ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ፌይኖርድ በሜዳው ኢንተርሚላንን ያስተናግዳል፡፡

ትናንት ምሽት በተደረጉ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች የወቅቱ የመድረኩ አሸናፊ ሪያል ማድሪድ በሜዳው ሳንቲያጎ ቤርናባው የከተማ ተቀናቃኙን አትሌቲኮ ማድሪድን አስተናግዶ በሮድሪጎ እና ብራሂም ዲያዝ ጎሎች 2 ለ 1 አሸንፏል፡፡

የእንግሊዙ ክለብ አርሰናል ወደ ኔዘርላንድ ተጉዞ ከፒኤስቪ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ከግማሽ ደርዘን በላይ ጎል በማስቆጠር 7 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.