Fana: At a Speed of Life!

ንቅሳት የካንሰር ተጋላጭነትን እንደሚጨምር ጥናት አመላከተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ንቅሳት የካንሰር ተጋላጭነትን እንደሚጨምር በደቡብ ዴንማርክ እና በሄልሲንኪ ዩኒቨርሲቲዎች የተደረገው ጥናት አመላክቷል።

በዩኒቨርሲቲዎቹ ተመራማሪዎች ይፋ የተደረገው አዲሱ ጥናት የንቅሳት ቀለም ለቆዳ ካንሰር እና ሊምፎማ ካንሰር ያለን ተጋላጭነት እንደሚጨምር አረጋግጠዋል።

የምርምር ቡድኑ የንቅሳት ቀለሞች ከተወጉበት አካባቢ በተጨማሪ ወደ ሌሎች የሰውነት አካባቢዎች እንደሚሰራጩም አመልክቷል።

ቀለሞቹ ሰውነትን ሊጎዱ ከሚችሉ ንጥረ ነገሮች ለመጠበቅ ወደ ሚረዱት እና ሊምፍ ኖድ ወደሚባሉ የሰውነት ክፍል ማለትም በአንገት፣ ብሺሺት፣ ብብት፣ ደረትና ሆድ አካባቢ በዕብጠት መልክ እንደሚቀመጡ ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል።

በዚህም ምክንያት የተከማቸው ዕብጠት ያልተለመደ የሕዋስ እድገትን ሊያስከትል እንደሚችል የተገለፀ ሲሆን በጊዜ ሂደት ወደ ካንሰር ሊያመራ እንደሚችል አብራርተዋል።

መጠኑ ትልቅ የሆነ ንቅሳት ያላቸው ግለሰቦች ምንም ንቅሳት ከሌለባቸው ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ የካንሰር ተጋላጭነቱ በሦስት እጥፍ ከፍ ያለ እንደሆነም በጥናቱ ተመላክቷል።

በደቡብ ዴንማርክ ዩኒቨርሲቲ የባዮስታስቲክስ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ሲርጌ ቤድስተድ ክሌመንሰን “ንቅሳቶች መጠናቸው በተለቀ እና ቆታቸው በጨመረ ቁጥር በሰውነት ውስጥ ብዙ ቀለም እንዲከማች ያደርጋሉ” ማለታቸውን የስካይ ኒውስ ዘገባ አመላክቷል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.