Fana: At a Speed of Life!

ዩክሬን ወደ ሰላም ድርድር ለመምጣት ዝግጁ እንደሆነች ማረጋገጧን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያ ዩክሬን የሰላም ስምምነትን ከግብ ለማድረስ ወደ ድርድር ጠረጴዛው ለመምጣት ዩክሬን ዝግጁ መሆኗን የሚገልጽ ደብዳቤ ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እንደደረሳቸው ገለጹ።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በዋሽንግተን በተካሄደው የጋራ ኮንግረስ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ይህን ደብዳቤ መላኩን አደንቃለሁ ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ባለፈው ሳምንት ወደ ኋይት ሃውስ አቅንተው ከትራምፕ እና ከምክትላቸው ጋር ያደረጉት ውይይት አለመሳካቱ ይታወሳል፡፡

ይህንን ተከትሎ በሀገራቸው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ዩክሬን በተቻለ ፍጥነት ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለመምጣት መዘጋጀቷን እና ከዩክሬናውያን በላይ ሰላም የሚፈልግ ማንም አለመኖሩን በደብዳቤው ስለመገለጹም ጠቁመዋል።

አክለውም ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ የማዕድን ስምምነትን ለመፈረም ዝግጁ መሆኑንም አሳውቆኛል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ዘለንስኪ ባለፈው ሳምንት ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር የተደረገው ውይይትን አስመልክቶ ሁኔታውን “አሳዛኝ” ብለው ቢጠሩትም በኋላ ግን ነገሮችን የማስተካከያ ወቅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሔለን ታደሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.