
አሜሪካ ከዩክሬን ጋር የምታደርገውን የደህንነት መረጃ ልውውጥ አቋረጠች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ ከዩክሬን ጋር ስታደርግ የቆየችውን የወታደራዊ ደህንነት መረጃ ልውውጥ ማቋረጧን አስታወቀች።
ዋሽንግተን እና ኬቭ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የወታደራዊ ደህንነት መረጃዎችን ሲለዋወጡ መቆየታቸው ተነግሯል።
የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የሁለቱ ሀገራት የደህንነት መረጃ ልውውጥ እንዲቋረጥ ውሳኔ ማሳለፉን የአሜሪካ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ማይክ ዋልዝ አረጋግጠዋል።
ውሳኔው ለምን ያህል ጊዜ ተግባራዊ እንደሚሆንና የደህንነት የመረጃ ልውውጡ በከፊል አልያም ሙሉ በሙሉ ስለመቋረጡ የተገለጸ ነገር የለም ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አሜሪካ ያለመግባባት የተቋጨውን የዶናልድ ትራምፕና የቮለድሚር ዘለንስኪ ውይይት ተከትሎ ከቀናት በፊት ለኬቭ የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ ማቋረጧም ይታወሳል።
ትናንት በዋሽንግተን በተካሄደው የጋራ ኮንግረስ ስብሰባ ላይ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባደረጉት ንግግር ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን የሚገልጽ ደብዳቤ መላካቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል።