በማዕድን ዘርፍ ያለውን ሕገ ወጥነት ለማስቆም ርምጃዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – አቶ ጌታቸው ረዳ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል በማዕድን ዘርፍ እየተስተዋሉ የሚገኙ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም እየተወሰዱ የሚገኙ ርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ገለፁ።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በመቀሌ ከተማ ከሰባት ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር በሰላምና ልማት፣ በሥራ እድል ፈጠራና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
በመድረኩም ወጣቶቹ በክልሉ ሰላምን ከማፅናት፣ ልማትን ከማፋጠን እንዲሁም ከመልካም አስተዳደር መስፈን ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ÷ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሰላምን የማፅናትና ልማትን የማስቀጠል እንዲሁም ሌሎች ጥያቄዎችን ለመመለስ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ እስከ ቀበሌ ያለውን መዋቅር በማጠናከር የተቋረጡ የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ወጣቶች ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን በመቆም የተጀመረውን ሰላም የማፅናትና ልማትን የማፋጠን እንቅስቃሴ ላይ ሊሳተፉና ሊደግፉ እንደሚገባም ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።