Fana: At a Speed of Life!

ለተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሀማት የሽኝት መርሐ-ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሀማት አፍሪካዊያን በአህጉሪቱ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም እንዲኖራቸው ለማስቻል ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን የአፍሪካ ህብረት ሰራተኞች ማኅበር ገለጸ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሠራተኞች ለተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሀማት የዕውቅና እና ሽኝት መርሐ ግብር አካሂደዋል።

የአፍሪካ ህብረት ሰራተኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ኑሁ ቲያም÷ ሙሳ ፋኪ ማሀማት በህብረቱ የሥራ ኃላፊነት ቆይታቸው የአፍሪካ ሀገራትን በማሰባሰብ በአህጉሪቱ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም እንዲኖራቸው ለማስቻል ብርቱ ጥረት ማድረጋቸውን አንስተዋል።

አዲስ የተመረጡት የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበርና ምክትልም የምንፈልጋትን አፍሪካ ለማየትና የጋራ ግቦችን ለማሳካት በትጋት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የተዋሃደች፣ የበለጸገችና ሰላማዊ አህጉር ለመፍጠር በሚደረገው ጥረትም የህብረቱ ሠራተኞች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሀማት÷ የህብረቱ ሠራተኞች ማኅበር ለሰጣቸው ዕውቅና ምስጋና አቅርበዋል።

በቢሊዮን ከሚቆጠሩ አፍሪካዊያን መካከል ህብረቱን ለመምራት መብቃት ዕድለኝነት ነው ያሉት ተሳናበቹ ሊቀመንበር÷ የህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎችና ድርጅቶች ላደረጉላቸው ትብብር ሁሉ ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ባለፉት ስምንት የአፍሪካ ህብረት የኃላፊነት ቆይታ ዓመታትም የአህጉሪቱን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በዚሁ ሂደት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሠራተኞች ላበረከቱት እገዛና ጉልህ አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።
ሙሳ ፋኪ ማሀማት እ.አ.አ ከ2017 እስከ 2025 ድረስ ህብረቱን በኮሚሽን ሊቀመንበርነት የመሩ ሲሆን፤ በ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የጅቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው ይታወቃል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.