ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እውን ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው – በለጠ ሞላ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ኢማኑኤል ምናሴ (ዶ/ር) ጋር በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
ምክክሩ የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራ አጋዥ በሆኑ መስኮች ላይ በጋራ በመስራት የዲጂታል ኢኮኖሚን ለማጎልበት ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።
በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከአጋር አካላት ጋር በትብብርና በቅንጅት በመስራት ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ ኢኮኖሚን ለመፍጠር እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ማፋጠንና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እውን ማድረግ ወሳኝ ጉዳያችን ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ በዲጂታል ኢኮኖሚው ላይ በትብብር በመስራት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ተጠቀሚነትና ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሁሉም ተሳትፎ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡
ኢማኑኤል ምናሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፍ የምታደርገው አበረታች ጥረት እንዲሳካ አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራን ለማሳለጥ በሚያስችለው ስነምህዳርና የሰው ኃይል ግንባታ ላይ ሰፊ ስራዎችን ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸውም ማንሳታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
የሁለትዮሽ ግንነኙነትን በማጠናከር በቀጣይ በዓለም አቀፍ ኢንዴክስ የሚወጡ ትክክለኛ የኢትዮጵያ መረጃዎች እና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ላይ ተቀራርበው እንደሚሰሩም ተስማምተዋል፡፡