በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሥድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ28ኛ ሣምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሥድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
በወጣው መርሐ-ግብር መሠረት 9 ሠዓት ከ30፤ ኖቲንግሃም ፎረስት በሲቲ ግራውንድ ስታዲየም ማንቼስተር ሲቲን ያስተናግዳል፡፡
በውድድር ዓመቱ አስገራሚ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው የአሰልጣኝ ኑኖ እስፕሪቶ ሳንቶ ቡድን ኖቲንግሃም ፎረስት፤ ደረጃውን ለማስጠበቅ ይፋለማል፡፡
በአንጻሩ የአሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላው ማንቼስተር ሲቲ በተመሳሳይ ሦስት ነጥብ በማግኘት ደረጃውን ለማሻሻል አልሞ ወደ ሲቲ ግራውንድ ያቀናል፡፡
እንዲሁም ምሽት 12 ሠዓት ላይ በሚደረጉ ጨዋታዎች ብራይተን ከፉልሃም፣ ክሪስታል ፓላስ ከኢፕስዊች ታውን፣ ሊቨርፑል ከሳውዝሃምፕተን ይገናኛሉ፡፡
በሌላ የጨዋታ መርሐ-ግብር ደግሞ ምሽት 2 ሠዓት ከ30፤ ብሬንትፎርድ ከአስቶንቪላ እንዲሁም ምሽት 5 ሠዓት ዎልቭስ ከኤቨርተን ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ሊጉን የአሰልጣኝ አርን ስሎቱ ሊቨርፑል በ67 ነጥብ ሲመራ፤ አርሰናል በ54 እንዲሁም ኖቲንግሃም ፎረስት በ48 ነጥብ በቅደም ተከተል 2ኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
ኢፕስዊች ታውን፣ ሌስተር ሲቲ እና ሳውዝሃፕተን ደግሞ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ክለቦች ናቸው፡፡
የሊቨርፑሉ ሞሃመድ ሳላህ በ25 ግቦች የኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱን ደረጃ ሲመራ፤ ኧርሊንግ ሃላንድ ከማንቼስተር ሲቲ በ20፣ አሌክሳንደር አይዛክ ከኒውካስል በ19 ግቦች እንዲሁም ክሪስ ውድ ከኖቲንግሃም ፎረስት በ18 ግቦች እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡