Fana: At a Speed of Life!

የሴቶች ቀን (ማርች 8) ሲታወስ…

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን ታሪካዊ መነሻ የሠራተኞች እንቅስቃሴ እንደሆነ ይገራል፡፡

በዚህ መነሻ የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ በአሁኑ ወቅት በተባበሩት መንግሥታት ዕውቅና አግኝቶ በየዓመቱ ይከበራል፡፡

የበዓሉ ጅማሮ በፈረንጆቹ 1908 ሲሆን፤ በወቅቱ 15 ሺህ ሴቶች በኒውዮርክ ከተማ “የሥራ ሠዓት ይሻሻል፣ የተሻለ ክፍያና ሴቶች በምርጫ መሳተፍ አለባቸው” በሚል የተቃውሞ ሰልፍ እንዳካሄዱ ይነሳል፡፡

ይህን ተከትሎም ከዓመት በኋላ የአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲ የመጀመሪያውን ብሔራዊ የሴቶች ቀን ዐወጀ።

ቀኑን ዓለም አቀፍ የማድረግ ሐሳቡ የመጣው በጀርመናዊቷ የሴቶች መብት ተሟጋቿ ክላራ ዜትኪን ሲሆን፤ ይህም በዴንማርክ ኮፐንሃገን በፈረንጆቹ 1910 የሴት ሠራተኞች ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ መሆኑን ታሪክ ያስረዳል፡፡

በጉባዔው የቀረበው ሐሳብም፤ ከ17 ሀገሮች በመጡ የሠራተኞች ማኅበራት፣ የሶሻሊስት ፓርቲዎች፣ የሴት ሠራተኞች ክበብ ተወካዮች በሙሉ ድምጽ ተቀባይነት ማግኘት ቻለ፡፡

በኮፐን ሀገኑ ጉባዔ ውሳኔ መሠረትም፤ በፈረንጆቹ መጋቢት 19 ቀን 1911 የሴቶች ቀን ሆኖ በኦስትሪያ፣ በዴንማርክ፣ በጀርመን እና በስዊዘርላንድ መከበር መጀመሩን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በዚሁ ዕለትም ከ1 ሚሊየን የሚልቁ ሴቶች እና ወንዶች ቀኑን አክብረው ውለዋል፡፡

የሴቶች ቀን ወደ መጋቢት 8 ቀን ተቀይሮ መከበር የጀመረው በፈረንጆቹ 1917 የዓለም ጦርነት አካባቢ የሩሲያ ሴቶች “ዳቦና ሰላም” በሚል ሰልፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ አንደሆነም ይቀሳል፡፡

በተጨማሪም በወቅቱ የነበረው ጊዜያዊ አሥተዳደር ሴቶች በምርጫ እንዲሳተፉ ፈቃድ መስጠቱ ምክንያት እንደሆነ ይነሳል፡፡

የሴቶች ቀን በይፋ በዓለም አቀፍ ደረጃ መከበር የጀመረው የተባበሩት መንግሥታት በዓሉን ማክበር በጀመረበት በፈረንጆቹ 1975 እንደሆነ ይገለጻል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በዓለም ላይ የሰፈነውን የተዛባ የሥርዓተ-ፆታ ኃይል ሚዛን ለማስተካከል በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ቀኑ ይከበራል፡፡

የሴቶች ቀን በተለያዩ ሀገራት የተለያየ የአከባበር እንድምታ አለው፡፡

ለምሳሌ፡- በሩሲያ ዕለቱ ሦስት ቀናት ሲቀሩት የአበቦች ሽያጭ ይደራል፤ በቻይና በዚያን ቀን ሴት ሠራተኞች ግማሽ ቀን ብቻ እንዲሠሩ ይፈቀዳል ፤ በጣሊያን ቀኑ ‘ላ ፌስታ ዴላ ዶና’ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ‘ሚሞሳ’ የተሰኘችውን አበባ ስጦታ በመለዋወጥ ይከበራል፡፡

እንዲሁም በአሜሪካ ሙሉ የመጋቢት ወር የሴቶች ታሪክ ወር የሚል ዕውቅና ተሰጥቷል፤ በሀገሪቱ መሪዎች ዘንድም ዕውቅና በተሰጠው በዚህ ወር የአሜሪካ ሴቶች አስተዋፅዖ ይዘከራል።

ሐምራዊ፣ አረንጓዴ እና ነጭ ቀለማት የሴቶች ቀንን ይወክላሉ የሚል ስምምነት አለ፡፡ በዚሁ መሠረትም፤ ሐምራዊዩ – ፍትሕንና ክብርን፣ አረንጓዴው- ልምላሜና ተስፋን እንዲሁም ነጩ ቀለም ንጽህናን ይወክላሉ፡፡

ይህ የቀለም ምርጫ የተደረገው በዩናይትድ ኪንግደም በፈረንጆቹ 1908 ነው፡፡

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ ሐሳብ በመከበር ላይ ነው፡፡

በአዲስዓለም ግደይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.