ማንቼስተር ዩናይትድ ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ28ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ማንቼስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድትራፎርድ አርሰናልን ያስተናግዳል።
ደካማ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘውና በሁሉም ውድድር ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድል ማድረግ የተሳነው ማንቼስተር ዩናይትድ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል።
ተጋጣሚው የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል በበኩሉ በሳምንቱ አጋማሽ ወደ ኔዘርላንድስ አቅንቶ ፒኤስቪ ላይ ከግማሽ ደርዘን በላይ ግብ አስቆጥሮ ካሸነፈበት ጨዋታ መልስ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ማንቼስተር ዩናይትድን ይገጥማል።
ማንቼስተር ዩናይትድ በሊጉ 33 ነጥብ በመሰብሰብ 15ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ አርሰናል በ54 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ቡድኖች በዚህ የውድድር ዓመት በኢምሬትስ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ አርሰናል 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።
የሁለቱን ቡድኖች ተጠባቂ ጨዋታ የ46 ዓመቱ እንግሊዛዊ ዳኛ አንቶኒ ቴለር በዋና ዳኝነት የሚመሩት ሲሆን÷በዛሬው ጨዋታ የማንቼስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች በክለቡ ባለቤቶች ላይ ተቃውሞ ያሰማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ በተመሳሳይ ሰዓት አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ ቼልሲ ከሌስተር ሲቲ እንዲሁም ቶትንሃም ሆትስፐር ከ ቦርንመዝ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በወንድማገኝ ጸጋዬ