ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ከ7 ሚሊየን ኩንታል በላይ ሲሚንቶ ለገበያ አቀረበ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን 7 ሚሊየን ኩንታል ሲሚንቶ ለገበያ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡
ፋብሪካው የገበያ ተደራሽነቱን ለማስፋትና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያለውን ተቀራርቦ የመስራት ባሕል ለማሳደግ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል፡፡
በዚህ ወቅትም የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የሲሚንቶ ምርት እጥረትና የሥርጭት ችግር በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስና ዋጋ በማረጋጋት ቀዳሚ ሚና እየተጫወተ መሆኑ ተገልጿል፡፡
አሁን ላይም በቀን 100 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ እያመረተ ሲሆን÷በዚህም በኢትዮጵያ 33 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሲሚንቶ አቅርቦት መሸፈን መቻሉ ተጠቁሟል፡፡
ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ በ2017 በጀት ዓመት የጥንካሬ ደረጃዎችን ካሳኩ አቻ ኢትዮጵያዊያን ምርቶች በጥራት ተሸላሚ መሆን መቻሉም ተመላክቷል፡፡
በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው ፋብሪካው ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊ እና ቋሚ የሥራ እድል መፍጠሩ ተጠቅሷል፡፡
በቀጣይም በመላ ሀገሪቱ ያለውን የሲሚንቶ ተደራሽነት ለማስፋፋት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡
በሲሳይ ጌትነት