Fana: At a Speed of Life!

የፆም የጤና ጥቅሞች

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች እና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጣቸው የጾም ወቅቶች ላይ እንገኛለን።

ፆም በበርካታ ህዝቦች የሚከወን እና በተለይም በሃይማኖታዊ ስነ ሥርዓቶች ላይ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ተግባር እንደሆነም የሃይማኖት አባቶች ያስተምራሉ።

ፆም ሃይማኖታዊ ሥርዓትን ተከትሎ የሚከወን ተግባር ሲሆን÷ ከምግብና መጠጥ ለተወሰነ ጊዜ ራስን በማራቅም ይተገበራል።

ከዚህ ቀደም የወጡ የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት÷ በቀን ከ16 እስከ 18 ሰዓት ምግብ ሳይመገቡ ማሳለፍ የተለያዩ የጤና በረከቶችን ያስገኛል።

በዚሁም ሰውነታችን አዳዲስ ሴሎችን ከመገንባት እና ጥሩ ጉልበት ከማግኘት አንፃር ጠቃሚ እንደሆነ ይገለፃል።

ፆም ከጤና አንፃር እንደ ያለንበት የሰውነት ክብደትና አቋም እንዲሁም የዕድሜ ክልል የተለያየ እንደሆነ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የሥነ ምግብ አማካሪዋ ቤተልሔም ላቀው ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ ከፆሙ የተሻለውን ጠቀሜታ ለማግኘት አንድ ምግብ ከተመገብን በኋላ ቀጣይ ለመመገብ 16 ሰዓታት ልዩነት ቢኖረው እንደሚመረጥ ጥናቶቹን በማንሳት አስረድተዋል።

ይህም ሰውነታችን አዳዲስ ሴሎችን የመቀየር ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነና 18 ሰዓታት ከሞላ ደግሞ በይበልጥ ሴሎቹ በፍጥነት ይታደሳሉም ነው ያሉት።

በተጨማሪም አንድ ነገር ላይ ትኩረት አድርገን የመከወን ብቃታችንን ከፍ እንደሚያደርገውም ጠቁመዋል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት÷ በፆም ወቅት ጨጓራን ጨምሮ ሌላው የአንጀታችን ክፍል ምግብን ከመፍጨትና ከማጓጓዝ አርፈው ትኩረቱን ያረጁ ህዋሳቶችን በማስወገድ ራሱን ወደ መጠገን ሥራ ይገባል።

ከዕይታ አንፃርም ሲታይ ፆም የተስተካከለ የሰውነት አቋም እንዲኖረን ያደርጋል የሚሉት ባለሙያዋ እንደ ስኳር የመሳሰሉ በሽታዎች ውጤታቸው እየወረደ እንዲመጣ እንደሚያደርገውም ጥናቶችን በመጥቀስ አስረድተዋል።

ከፆም በኋላም ለመፈጨት ቀላል የሆኑ ምግቦችን መመገብ አስፈላጊ እንደሆነም መረጃዎች ያሳያሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.