የእናቶችና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ የተጀመረው ሥራ እንዲጠናከር ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የእናቶችና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ የጤና ሙያ ማህበራት የተጀመሩ ሥራዎችን እንዲያጠናክሩ የጤና ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል።
የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሐኪሞች ማህበር 33ኛ ዓመታዊ ጉባዔውን እያካሄደ ነው፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት÷መንግስት የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ባከናወነው ተግባር አበረታች ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል፡፡
ለዚህም የጤና አገልግሎቱን የሚያሻሽሉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ነው የገለጹት፡፡
ከአጋር አካላትና ከጤና ሙያ ማህበራት ጋር ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር ፍትሃዊና ደህንነቱ የተጠበቀ የሕክምና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለም አመልክተዋል።
እንደ ሀገር የእናቶችንና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ እየተከናወነ ባለው ሥራ የሙያ ማህበራት ሚና ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመው÷የሚያከናውኑትን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ መጠየቃቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።