በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ በተከናወኑ ሥራዎች ተጨማሪ 310 ሜጋ ዋት ኃይል ማግኘት ተቻለ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት አምስት ዓመታት በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ በተከናወኑ የአቅም ማሳደግና የማዘመን ሥራዎች ተጨማሪ 310 ሜጋ ዋት ኃይል ማግኘት መቻሉን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
በተቋሙ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ ዳይሬክተር ጋሻው እንድሪያስ እንዳሉት÷ ከከተሞችና ከኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ ነው።
በዚህም አዳዲስ የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ በተጨማሪም ነባር የማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም የማሳደግ፣ የማስፋፊያ እና ማዘመን ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በነባር ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ 22 የሚሆኑ ‘ፓወር ትራንስፎርመሮችን’ በመትከል 310 ሜጋ ዋት ተጨማሪ ኃይል ማግኘት እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡
የጣቢያዎቹን የመቆጣጠሪያ ብሬከሮች አቅም የማሳደግና የማዘመን ሥራዎች በመሠራታቸው ትራንስፎርመሮቹ በተሻለ አቅም እንዲሠሩ ማድረግ መቻሉንም መናገራቸውን የተቋሙ መረጃ አመላክቷል፡፡
በ75 ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ለማከናወን ከታቀዱት የመቆጣጠሪያ ብሬከር ቅየራ ሥራዎች እስካሁን የ25ቱ መጠናቀቁን የጠቆሙት አቶ ጋሻው÷ በተያዘው ዓመት የአስር ጣቢያዎችን ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡