በጎ ፈቃደኞች እና ባለ ሃብቶች ለምገባ መርሐ-ግብር የሚያደርጉትን እገዛ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጎ ፈቃደኞች እና ባለ ሃብቶች ለምገባ መርሐ-ግብር የሚያደርጉትን እገዛ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ ጥሪ አቀረበ።
ኤጀንሲው እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር እየተወያየ ነው።
በመርሃ ግብሩ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሽታዬ መሃመድ፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት በትምህርት ቤቶች እና በማዕከላት የምገባ መርሐ-ግብር ሲከናወን ቆይቷል ብለዋል።
መርሐ-ግብሩ የወላጆችን ጭንቀት እና የተማሪዎችን ሰቀቀን በመቀነስ በጎ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በዚህም 834 ሺህ ተማሪዎችን በቀን ሁለት ጊዜ መመገብ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን እና በ22 የምገባ ማዕከላት 36 ሺህ 600 አቅመ ደካማ አረጋዊያንን መመገብ የተቻለበት አቅም መፈጠሩ ተመላክቷል።
በዚህ የኤጀንሲው ተግባራት ውስጥ በጎ ፈቃደኞች እና ባለ ሃብቶች የሚያደርጉት እገዛ የሚበረታታ እንደሆነና በቀጣይም በተሻለ መንገድ መቀጠል እንዳለበት ዋና ዳይሬክተሯ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ከተማ አስተዳዳሩ የሚያከናውነው የምገባ መርሐ-ግብር የስራ እድል ፈጠራን ጭምር ማሳደግ የቻለ መልከ ብዙ እፎይታ መፍጠሩ ተመላክቷል።
በውይይት መድረኩ የኤጀንሲው መለያ ሎጎ ይፋ ሆኗል።
በይስማው አደራው