Fana: At a Speed of Life!

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኮሙኒኬሽን ዘዴ ልምድ በማካፈል ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኮሙኒኬሽን ዘዴ በልዩ አተያይ ሐሳቦችን፣ የሥራ ተነሳሽነትን የሚፈጥሩ ልምዶችንና ተግባራትን በማካፈል ላይ ያተኮረ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከክልሎች የሚገኙ የሥራ ሪፖርቶችን ለሌሎች የተነሣሽነት ምንጭ እንዲሆኑ ሲያጋሩ መቆየታቸውንና ላለፉት ሰባት ዓመታት ለየት ባለ መንገድ ግልጽነትና ተደራሽነትን በማለም የኮሙኒኬሽን ስራው መከናወኑን ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡

በዚህ ሂደት የክልሎች የሥራ ለውጦች ጎላ ብለው እንዲታዩ በማድረግ ምርጥ ተመክሮዎች እና ስኬቶች በሌሎች ከፍ ተደርገው እንዲሰሠሩ እገዛ ማድረጋቸው ተገልጿል።

ይሁንና ከታችኛው የአስተዳደር እርከን ጀምሮ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ መረጃዎች በሚላኩበት ሂደት አንዳንድ ትክክል ያልሆኑ አቀራረቦች በተለያየ እርከን በሪፖርቶች ሊካተቱ መቻላቸውን ጽ/ቤቱ ገልጿል፡፡

ለአብነትም በትናንትናው ዕለት በተጋራው መልዕክት የተወሰኑ ምስሎች ከመስክ ከተገኙ እውነተኛ ፎቶዎች ጋር ተቀላቅለው ከክልል ከነበረ ልውውጥ እስከ ፌደራል ደረጃ መድረሳቸውን ጠቅሷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በጉዳዩ ላይ ባወጣው መረጃ፡ በመረጃ ልውውጥ ሂደት ስህተት ዳግም እንዳይፈጸም ተገቢ ርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑንም አስታውቋል።

ምስሎቹን የያዘው ልጥፍ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ የትሥሥር ገጽ የተነሣ መሆኑን ጠቅሶ፤ ርምት እንዲወሰድ ላሳወቁ ዜጎችም ምስጋና አቅርቧል።

ትክክለኛውን መረጃና አቀራረብ የያዙ የተምሳሌታዊው ምርት ሥራ ዘገባዎች በቀጣይ ሚዲያዎች እንደሚቀርቡም አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.