Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት ቁልፍ አጋር ሆና መቀጠሏ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአውሮፓ ሕብረት ቁልፍ አጋር ሆና መቀጠሏን በኢትዮጵያ የሕብረቱ አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር ገለጹ።

መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላይ ያደረጉ የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር የሕብረቱ አባል ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር በሰላምና ደህንነት፣ ሽብርተኝነትን በመከላከል እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ተቀራርበው በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

21 የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት በአዲስ አበባ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመው÷ ትብብራቸውን ለማጠናከር እና በቀጣይም በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አንስተዋል።

ባለፉት በርካታ ዓመታት የሕብረቱ አባል ሀገራት የኢትዮጵያ ጠንካራ እና አስተማማኝ አጋር ሆነው መቀጠላቸውን እና በጋራ በየዓመቱ ወደ 1 ቢሊየን ዩሮ የሚጠጋ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም አስታውሰዋል።

ሕብረቱ ከሰሞኑ በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል በአንካራ የተደረሰውን ስምምነት እንደሚያደንቅ እና የፕሪቶሪያውን ስምምነት እየተከታተለ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

ተግባራዊ የተደረገውን የኢኮኖሚ ሪፎርም የአውሮፓ ሕብረት እንደሚደግፍ ገልጸው÷ በርካታ አባል ሀገራት የኢንቨስትመንት ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ፍላጎት ማሳየታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.