ቻይና ለኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለች – አምባሳደር ቼን ሀይ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና ለኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ እድገትና ሽግግር ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሀይ ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ እና በቻይና ሚዲያ ግሩፕ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
አምባሳደር ቼን ሀይ በዚህ ወቅት÷ ቻይና እና ኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂ ሽግግር እስከ መሠረተ ልማት አውታሮች መስፋፋት አብረው ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስተው÷ በቀጣይነትም ያላትን ሁሉን አቀፍ አጋርነት አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
ቻይናዊያን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸው÷ በቀጣይ እንደ ማዕድንና ኢንዱስትሪ ልማት ባሉ ዘርፎች ባለሃብቶች ገብተው መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ እንዲያደርጉ ይሰራልም ነው ያሉት።
በአፍሪካ – ቻይና ግንኙነትም ቤጂንግ የአፍሪካ ሀገራት ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ እያደረገች አንደምትገኝና ይህም ቀጣይነት እንደሚኖረው አመላክተዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሀጽዮን በበኩላቸው÷ ባለፉት ዓመታት ሁለቱ ሀገራት ሁሉን አቀፍ ግንኙነት እንደነበራቸው አስታውሰው÷ ቻይና ኢትዮጵያ ውስጥ ከ8 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ በሆነ ገንዘብ 3 ሺህ 300 ፕሮጀክቶች ላይ መሳተፏን ጠቁመዋል።
የልማት አጋርነቷንም የጋራ በሆኑ መስኮች አጠናክረን መቀጠል እንፈልጋለን ሲሉ ተናግረዋል።
በአሸብር ካሳሁን