ባለ ብዙ ዘርፍ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለመገንባት የቀረበው ጥያቄ በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገባ ውሳኔ ተላለፈ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ባለ ብዙ ዘርፍ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለመገንባት የቀረበው ጥያቄ በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገባ ውሳኔ አስተላልፏል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ቦርዱ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን በመገምገም ተወያይቶ ውሳኔ ከሰጠባቸው አጀንዳዎች ውስጥ አንዱ ከ78 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ካፒታል በመመደብ ባለ ብዙ ዘርፍ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለመገንባት በግል ባለሀብት በቀረበው ጥያቄ ላይ እንደሆነም ተገልጿል።
በጥያቄው ላይ ቦርዱ በስፋት ከተወያየ በኋላ ባለ ብዙ ዘርፍ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሆኖ እንዲሰየም እና ጥያቄ አቅራቢዎቹም በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ውሳኔ አሳልፏል።
በተጨማሪም የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አሰያየም፣ የመሬት አመዳደብ እና አጠቃቀም መመርያን ጨምሮ በቀረቡለት ሌሎች ጉዳዮች ላይ በመወያየት ውሳኔ መስጠቱን ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
ቦርዱ በሀገሪቱ ውስጥ ምቹ እና ሳቢ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት እና ለኮሚሽኑ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።