Fana: At a Speed of Life!

ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግስታት የመንገድ ደህንነት ፈንድ የቦርድ አባል ሆነው ተሾሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግስታት የመንገድ ደህንነት ፈንድ (ዩኤንአርኤስኤፍ) የቦርድ አባል ሆነው ተሾመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራዊ የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ በመቅረፅና የመንገድ ደህንነት ትምህርት በስርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት  በማድረግ የወሰደችው እርምጃ የመንገድ ደህንነትን ለማስፈን ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ለሚኒስትሩ በተፃፈው የሹመት ደብዳቤ ተገልጿል፡፡

በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ስራዎች የተገነቡ ምቹ የብስክሌትና የእግረኛ መንገዶች እንዲሁም የተሻሻሉ የመንገድ ትስስር ስራዎች እንደ ሀገር የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ቅንጅትን የሚያሳድጉ መሆናቸውም በደብዳቤው ተጠቁሟል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ኢትዮጵያ በመንገድ ደህንነት ላይ ያላትን ቁርጠኝነትና የምታደርገውን ጥረት በመገንዘብና እውቅና በመስጠት ዓለሙ ስሜን (ዶ/ር) በዩኤንአርኤስኤፍ ስር የባለአደራዎች ቦርድ የቦርድ አባል ሆነው መሾማቸውን አሳውቋል፡፡

የሚኒስትሩ በቦርድ አባልነት መሾም ኢትዮጵያ ልምዷን ለሌሎች ሀገራት እንድታጋራና ከመላው ዓለም በመንገድ ደህንነት ላይ የተሻሉ ተሞክሮዎችን እንድታገኝ  መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር እንደሆነም የትራስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ዩኤንአርኤስኤፍ  በፈረንጆቹ 2018 ሚያዚያ ወር ላይ የተመሠረተ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጠቀሜታ ላላቸው ፕሮጀክቶች ተጨማሪ ገንዘብ የማሰባሰብ እና የመደገፍ ስራን የሚሰራ ተቋም ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.