Fana: At a Speed of Life!

በሻምፒየንስ ሊጉ አትሌቲኮ ማድሪድ ከሪያል ማድሪድ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ አትሌቲኮ ማድሪድ ከሪያል ማድሪድ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡

የሻምፒየንስ ሊጉ የ16ቱ ጥሎ ማለፍ የመልስ ጨዋታዎች ቀጥለው ሲደረጉ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ በሜዳው የከተማ ተቀናቃኙን ሪያል ማድሪድን ምሽት 5 ሠዓት ላይ ያስተናግዳል።

በሁሉም ውድድር ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደው ባለ ሜዳው አትሌቲኮ ማድሪድ ወደ ድል ለመመለስ እና ቀጣዩን ዙር ለማለፍ ይፋለማል።

ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድር እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ አንድ ጊዜ ድል የቀናቸው ሲሆን በሦስቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

በሪያድ ኤር ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም የሚደረገውን ተጠባቂ የመልስ ጨዋታ ፖላንዳዊው ዳኛ ሲሞን ማርሲንያክ በመሐል ዳኝነት የሚመሩት ሲሆን፤ የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ በሪያል ማድሪድ 2 ለ 1 አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል።

የሁለቱ ቡድኖች የድምር ውጤት አሸናፊ በሩብ ፍፃሜው ከአርሰናል እና ፒኤስቪ አሸናፊ ጋር ይገናኛል።

በተመሳሳይ ምሽት 5 ሠዓት ላይ የእንግሊዙ ክለብ አርሰናል ከፒኤስቪ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።

በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ አርሰናል ወደ ኔዘርላንድስ አቅንቶ ተጋጣሚው ፒኤስቪ ላይ ከግማሽ ደርዘን በላይ ጎል በማስቆጠር 7 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፎ መመለሱ ይታወሳል።

ሌላኛው በመድረኩ እንግሊዝን የሚወክለው አስቶንቪላ በሜዳው ቪላ ፓርክ ክለብ ብሩዥን ምሽት 5 ሠዓት ላይ ያስተናግዳል።

በአሰልጣኝ ኡናይ ኢምሬ የሚመሩት ቪላዎች፤ የመጀመሪያውን ዙር ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ ተጉዘው 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፋቸው አይዘነጋም።

የሁለቱ ቡድኖች የድምር ውጤት አሸናፊ በሩብ ፍፃሜው ከፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ ጋር ይገናኛል።

ከነዚህ ጨዋታዎች አስቀድሞ ምሽት 2 ሠዓት ከ 45 ላይ የፈረንሳዩ ክለብ ሊል ቦርሲያ ዶርትሙንድን በሜዳው ያስተናግዳል።

ሁለቱ ቡድኖች በሲግናል ኤዱና ፓርክ ያደረጉትን የመጀሪያ ዙር ጨዋታ 1 አቻ በሆነ ውጤት ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።

ትናንት ምሽት በተደረጉ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የአስራ ስድስቱ ጥሎ ማለፍ የመልስ ጨዋታዎች፤ ባየርን ሙኒክ፣ ፒኤስጂ፣ ባርሴሎና እና ኢንተር ሚላን ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል።

በወንድማገኝ ፀጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.