የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር የቀጥታ ኤሌክትሪክ መስመር ተጠቃሚ ሆነ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር የቀጥታ ኤሌክትሪክ መስመር ተጠቃሚ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
ለኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ 39 ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ የቀጥታ ኤሌክትሪክ መስመር መዘርጋቱም ነው የተገለጸው።
በአገልግሎቱ የሸገር ሪጅን እንዳስታወቀው÷ምድር ባቡሩ ከአሁን በፊት የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ያጋጥመው የነበረ ሲሆን አሁን ላይ መስመሩ በመዘርጋቱ ኅብረተሰቡ አስተማማኝ እና ያልተቆራረጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ አስችሏል፡፡
የቀጥታ መስመር ከገላን የኃይል ማሰራጫ የተዘረጋ 11 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለውና 226 ኮንክሪት ምሰሶ ተከላ እንደተከናወነም ተገልጿል፡፡
የተዘረጋው የቀጥታ መስመር በዋነኝነት ተጠቃሚ የሚያደርገው አኖሌ ተብሎ ለሚጠራው ምድር ባቡሩ ጣቢያ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ አመላክቷል፡፡