በአማራ ክልል በቀሪ እርጥበት ከለማ መሬት ከ7 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተገኘ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የክረምቱን መውጣት ተከትሎ በቀሪ እርጥበት በተለያየ ሰብል ከለማው ከ334 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ከ7 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ እንዬ አሰፋ፤ በቀሪ እርጥበት የለማው የሰብል ምርት በክልሉ የምግብ ሉአላዊነት ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥረት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
አፈጻጸሙ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 3 ሚሊየን 182 ሺህ ኩንታል ምርት ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ ብልጫ እንዳለው ጠቁመው፤ በልማቱ ከአንድ ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
የዝናቡ መውጫ ወቅት መራዘም ገብስና ስንዴን ጨምሮ ለሰብሎች ፍሬ አያያዝ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ለምርቱ መጨመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ማስረዳታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።