ከቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት ወጪ ንግድ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በላይ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ስምንት ወራት 269 ሺህ 114 ነጥብ 42 ቶን የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት ለውጪ ገበያ በማቅረብ 1 ቢሊየን 235 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገለጸ፡፡
አፈጻጸሙ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር፤ በ112 ሺህ 618 ነጥብ 66 ቶን እና በ512 ነጥብ 71 ሚሊየን ዶላር ብልጫ ማሳየቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አረጋግጧል፡፡
በሥምንት ወራት ውስጥ 257 ሺህ 248 ነጥብ 79 ቶን ቡና ለውጪ ገበያ ተልኮ፤ 1 ቢሊየን 226 ነጥብ 8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የባለስልጣኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
ይህ አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር፤ በ106 ሺህ 818 ነጥብ 24 ቶን እና በ510 ነጥብ 48 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ጭማሪ ማሳየቱም ተጠቅሷል፡፡