በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ29ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር ለቀጣይ ዓመት የአውሮፓ መድረክ ተሳትፎ ወሳኝነት ያላቸው ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
የቀጣይ ዓመት የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎን ለማግኘት የሚያልሙት ማንቼስተር ሲቲዎች ምሽት 12 ሰዓት ላይ በኢቲሃድ ብራይተንን የሚያስተናግዱበት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
በ47 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቼስተር ሲቲ በኖቲንግሀም ፎረስት ከተሸነፈበት ጨዋታ መልስ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል።
ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት ያላስተናገደው ተጋጣሚው ብራይተን በበኩሉ አሸናፊነቱን ለማስቀጠል እና በሚቀጥለው የውድድር ዓመት በአውሮፓ መድረክ ለመሳተፍ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ለመቆየት ይፋለማል።
በሌላ የሊጉ ጨዋታ ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ኖቲንግሀም ፎረስት ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ወራጅ ቀጣና ላይ ከሚገኘው ኢፕስዊች ታወን ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።
በ51 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ፎረስት የዛሬውን ጨዋታ የሚያሸንፍ ከሆነ ነጥቡን ወደ 54 ከፍ በማድረግ ከአርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ዝቅ ያደርጋል።
ኤቨርተን ከዌስትሀም ዩናይትድ እንዲሁም ሳውዛምፕተን ከ ዎልቭስ ምሽት 12 ሰዓት ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።
ቦርንመዝ ከብሬንትፎርድ ምሽት 2፡30 ላይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
ሊጉን ሊቨርፑል በ70 ነጥብ ሲመራው አርሰናል በ55 እንዲሁም ኖቲንግሀም ፎረስት በ51 ነጥብ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ወራጅ ቀጣናው ላይ ኢፕስዊች ታወን ፣ሌስተር እና ሳውዛምፕተን ተቀምጠዋል።
በወንድማገኝ ጸጋዬ