ብቁ የሰው ኃይል ከማፍራት ባሻገር ለጥራት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብቁና ተወዳዳሪ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ርብርብ ከማድረግ ባሻገር ለጥራት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴሩ ለተጠሪ ተቋሟት የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን ከኢንስቲትዩቱ ጋር የተፈራረሙት 46 የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት እና የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ኤጀንሲዎች መሆናቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ተጠሪ ተቋማቱን ጨምሮ በተዋረድ ያለው መዋቅር የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን እንዲተገብሩ የሚያስችሉ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
በእስካሁኑ ሂደትም ሰባት የሚሆኑ የስልጠና ተቋማት የዓለም አቀፉ የትምህርት ተቋማት ሥራ አመራር ሥርዓትን በማሟላት እውቅና እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንድማገኝ አሰፋ በበኩላቸው፤ በጥራት ሥራ አመራር እውቅና ካገኙ ተቋማት የሚመረቁ ባለሙያዎች የተሻለ አቅም እና ተቀባይነት እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡