2ኛ ጠቅላላ ጉባዔው ብልፅግና ፓርቲ ያለውን ምርጥ ሀሳብ ያስተዋወቀበት ነበር – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ ጠቅላላ ጉባዔው ከኢትዮጵያ ባሻገር ለአፍሪካና ለሰው ልጅ በሙሉ ያለውን ምርጥ ሀሳብ ያስተዋወቀበት እንደነበር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
ለብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓልና 2ኛ ጠቅላላ ጉባዔ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የዕውቅና መርኃ ግብር ተካሂዷል፡፡
በመርኃ ግብሩ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ እንደተናገሩት፤ 2ኛ ጠቅላላ ጉባዔው ስኬቶችን፣ ፈተናዎችን እና ለቀጣይ መነሳሳትን የሚፈጥሩ ሀሳቦችን በመለየት ተጠናቋል፡፡
ትልቅ ፋይዳ ባስገኘ መልኩ የተጠናቀቀው ጉባዔው የፓርቲና የህዝብ ግንኙነት የተጠናከረበት እንደነበርም አንስተዋል፡፡
ከተጀመሩ ስኬቶች ባሻገር የኑሮ ውድነትን፣ የስራ አጥነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አቅጣጫዎች የተቀመጡበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በጉባዔው በፖርቲው አሰራር መሰረት ሰርተው የሚያሰሩ አመራሮች ተመርጠዋልም ነው ያሉት፡፡
በምንይችል አዘዘው