በወላይታ ዞን ዳሞት ወይዴ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ15 ሰዎች ህይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በወላይታ ዞን ዳሞት ወይዴ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ15 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ።
የትራፊክ አደጋው በዛሬው ዕለት አመሻሽ አከባቢ የተከሰተ ሲሆን፥ 46 ሰዎችን ባሳፈረው የሕዝብ ማመላለሻ መኪና ላይ በተፈጠረው የቴክኒክ ብልሽት ምክንያት ፍሬን ተበጥሶ እንደሆነ የዳሞት ወይዴ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር ይስሀቅ ቦሻ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።
አደጋው በወረዳው በዴሳ ከተማ ውስጥ በሚገኘው በዴሳ ወንዝ ተገልብጦ የደረሰ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአደጋው እስካሁን የ15 ሰዎች ህይወት ማለፉንና 21 ከባድ ጉዳት እንዲሁም 6 ቀላል ጉዳት መድረሱን ጠቁመው፥ 5 ሰዎች ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን አመላክተዋል።
አደጋው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም በወላይታ ሶዶ ኦቶና እና ክርስቲያን ሆስፒታሎች ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
መኪናው ከአርባምንጭ ዝጊቲ አቦ ዓመታዊ ንግስ በዓል እየተመለሱ የነበሩ የሻሸመኔ ከተማ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ወጣቶችን አሳፍሮ ሲጓዝ እንደነበረም ተመላክቷል።
በአድማሱ አራጋው