Fana: At a Speed of Life!

የህወሓት አንጃ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዳይተገበር እንቅፋት ከመሆን እንዲቆጠብ ትዴፓ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የህወሓት አንደኛው አንጃ የፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት እንዳይተገበር እንቅፋት ከመሆን እንዲቆጠብ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) አሳሰበ፡፡
ፓርቲው የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የፓርቲው ሊቀ መንበር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) በአንደኛው የህወሓት አንጃ የሚከናወነው ድርጊት በህዝባችን ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የህዝብ ፍላጎት ያስከበረና ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኙ በር የከፈተ ታሪካዊ ስምምነት መሆኑን በመግለጫው ላይ አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ቡድኑ በስልጣን ዘመኑ ያካበተውን ሃብት አጣለሁ ከሚል ፍራቻ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በተሟላ መልኩ እንዳይተገበር እንቅፋት እየፈጠረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የህወሓት አንጃ ከዚህ አካሄዱ ሊቆጠብ ይገባል ሲሉ የፓርቲው ሊቀ መንበር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡
የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትሎ በተለያየ መንገድ በትግራይ ህዝብ ላይ ጫና የሚያሳድሩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
የህዝቡ ፍላጎት ሰላምና ልማት መሆኑን ገልጸው፤ የፌዴራል መንግስት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ስምምነቱ የሚመለከታቸው የዓለም አቀፍ ተቋማትና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካና ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገንቢ ሚና መጫወት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.