Fana: At a Speed of Life!

ለምግብነት መዋል የሌለበትን ጨው ሲያመርቱ የነበሩ በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል ሀዋሳ እና ለኩ ከተሞች ለምግብነት መዋል የሌለበትን ጥሬ ጨው በድብቅ ሲያመርቱ እጅ ከፍንጅ የተያዙ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ፡፡

በህገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩት ሸጋ፣ ሺማና ልዩ አዮዳይዝድ ጨው በሚል ህገወጥ የንግድ ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ገልጿል፡፡

ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በተደረገ ክትትል በህገወጥ መንገድ ተመርቶ ለህብረተሰቡ ሊሰራጭ ለምግብነት የማይውል ጨውና በተለያየ የንግድ ስም የተዘጋጁ ማሸጊያዎች መገኘታቸውን የባለስልጣኑ የሃዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

በህገወጥ የጨው ምርትና አቅርቦት ላይ የተሳተፉት አካላት በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የክልሉ የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብዓቶች ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

ህገወጥ የጨው አምራቾችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተደረገው ኦፕሬሽን ህብረተሰቡ ላደረገው ትብብር ጽ/ቤቱ ምስጋና አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ባካሄደው የድህረ ገበያ ጥናት በህገወጥ መንገድ ተመርተው ወደ ገበያ ሲሰራጩ የነበሩ 44 ዓይነት የገበታ ጨው ምርቶች ህብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸው ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.