Fana: At a Speed of Life!

በሞጆና አዳማ ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን የኃይል መቆራረጥ የቀነሰ ሥራ መሰራቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሞጆና አዳማ ከተሞች የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን የኃይል መቆራረጥ የቀነሰ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ሥራ መሰራቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአዳማ ሪጅን አስታወቀ።

በከተሞቹ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሚቀርበውን የኃይል አቅርቦት አስተማማኝና ጥራት ያለው ለማድረግ እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል።

የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ጠሃ አህመድ እንደገለጹት፤ በስምንት ወር ውስጥ በሞጆ ከተማ የ35 ነጥብ 6 ኪ.ሜ እንዲሁም በአዳማ ከተማ 28 ነጥብ 5 ኪ.ሜ የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ መከናወኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ለወለንጪቲ የ23 ኪ.ሜ እና ለዲክሲስ ከተማ 11 ነጥብ 4 ኪ.ሜ የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ መጠናቀቁን ገልጸው በመስመር ዝርጋታው ከ1 ሺህ 500 በላይ የምሶሶ ግንባታ መከናወኑን አብራርተዋል።

የተገነቡት የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች በሞጆ እና በአዳማ በሚገኙ 20 አምራች ኢንዱስትሪዎች ይገጥም የነበረውን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለመቀነስ አግዟል ብለዋል፡፡

አክለውም የኃይል መቆራረጥ ችግርን ለመቀነስ ብሎም ዜሮ ለማድረስ የሚያስችል ስራ መጠናቀቁን የአገልግሎቱ መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.