የጣና ዳር ንግሥቷ ባሕር ዳር በፍጹም የሰላም ድባብ ልማቷን እያፋጠነች ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጣና ዳር ንግሥቷ፤ባለዘንባባዋ ሙሽራ ውቧ ከተማ ባሕር ዳር በፍጹም የሰላም ድባብ ልማቷን እያፋጠነች ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷የጣና ዳር ንግሥቷ፣ባለዘንባባዋ ሙሽራ እና የቱሪዝም አስኳሏ ባሕር ዳር ስራ ላይ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ፍፁም የሰላም አየር፣ የዓይንና የመንፈስ ማረፊያ ውብ ሥፍራ የታደለችው ባሕር ዳር ÷ከመዝናኛ እስከ ግዙፍ የንግድ ሥፍራዎቿ በእንቅስቃሴ ተሞልተዋል፤ ሀገሬው ከጧት እስከ ማታ ሥራ ላይ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ከልጅ እስከ አዋቂ በልዩ ልዩ ስፖርቶች ደምቀዋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ከዚሁ ጎን ለጎን ግዙፉ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ከተማዋን የስፖርት ቱሪዝም ማዕከል የሚያደርጋት ይሆናል ብለዋል።
ሀገሬው በሥራ የደከመ አካሉንና አዕምሮውን ለማደስ ስፖርት ሲሠራ፣ በመዝናኛ ማዕከላት ሲዝናና፣ በዘንባባዋ ጥላ ስር አረፍ ሲል፣ በጣና ዳርቻ ሰብሰብ ብሎ ሲጫወት፣ በምሽት በእግር ሲንቀሳቀስ ማየት ልብን ሀሴት ያወርሳል ነው ያሉት።
ወቅቱ የዐቢይና የረመዳን አፅዋማት የሚጾሙበት ነው፤የከተማዋ ምዕመን ሰርክ ወደ መስጅድና ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሲተምም ማየት መንፈሳዊ ኩራትን ይፈጥራል ሲሉም ገልጸዋል።
ውቧ ከተማ ልማቷን እያፋጠነች፤ ፍፁም የሰላም ድባብ፤ እረፍት አልባ የልማት ሥራ፤ ሞቅ ያለ የመዝናኛና የንግድ እንቅስቃሴ የሚታይባት መሆኗንም አስገንዝበዋል፡፡
በጉብኝታቸው የሠላም ንፋስ፣ የልማትና የሥራ ጥድፊያ እንዲሁም የቱሪዝም መነቃቃት መደሰታቸውን ገልጸው÷ የተጀመሩ ሥራዎችን ዓይናችንን ሳንነቅል በተገቢው ጥራት እንዲጠናቀቁ ክትትላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡