Fana: At a Speed of Life!

ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ ወዲህ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል – ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ወዲህ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሯ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ከህብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ቀርበው ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት የተዘጉ ፋብሪካዎች ስለመኖራቸው የተጠየቁት ሚኒስትሯ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ለኢንዱስትሪዎች መዋቅራዊ ችግር የሚሆንበት ሁኔታ እንደሌለ አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ወዲህ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

የሸቀጦች የወጪ ንግድ የውጭ ምንዛሪ አንዱ ምንጭ መሆኑን ገልጸው፤ ባለፉት ሰባት ወራት ለውጭ ገበያ የቀረበው የምርት መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ102 በመቶ መጨመሩን አብራርተዋል፡፡

ለአምራች ኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆኑ የካፒታል እቃዎች አቅርቦት ከአምናው አንጻር በ20 በመቶ ማደጉን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ከልማት አጋሮች ባለፉት ሰባት ወራት 3 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር መገኘቱንና ከውጭ ከተላከ ገንዘብ (ሬሚታንስ) የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት የ14 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

ብሔራዊ ባንክ ጨረታ በማካሄድ የውጭ ምንዛሪ ለገበያ ማቅረቡን ያስታወሱት ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፤ በዚህም መሰረት ባንኮች 5 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 4 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር መሸጣቸውን ገልጸው፤ በባንክ ስርዓት ውስጥ 720 ሚሊየን ዶላር ትርፍ በመኖሩ አሁን ላይ የውጭ ምንዛሪ አዋጭ ለሆኑ ኢንቨስትመንቶች ችግር የሚሆንበት ሁኔታ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታምርት እንቅስቃሴ አማካኝነት በሀገራዊና ዓለም አቀፍ ችግሮች ምክንያት ምርት አቁመው የነበሩ 395 ፋብሪካዎች ያጋጠሟቸውን ችግሮች በመፍታት ዳግም ስራ እንዲጀምሩ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.