Fana: At a Speed of Life!

የጤና አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው – ዶ/ር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጤና ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አዘጋጅነት በጤናው ዘርፍ ከሕብረተሰቡ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም አሁን ላይ በኢትዮጵያ መከላከል እና አክሞ ማዳን ፖሊስ ላይ የተመሰረተ ሁሉን አቀፍ ጤና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አብዛኛው የሕክምና አገልግሎት በሀገር ውስጥ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው÷ወደ ውጪ ሀገራት በመሄድ የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙ ዜጎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

ተላላፊ ለሆኑና በሀገር ውስጥ አቅም መታከም ለሚችሉ ሕመሞች በሀገር ውስጥ ሕክምና እንደሚሰጥ ያስረዱት ሚኒስትሯ÷ በአንጻሩ ተላላፊ ያልሆኑና ውስብስብ የጤና እክል ያለባቸው ዜጎች በውጪ ሀገራት እንዲታከሙ ይደረጋል ብለዋል፡፡

82 ከሞቶ የሚሆነው ሕዝብ በመንግስት የጤና ተቋማት ሕክምና እንደሚያገኝ ጠቁመው÷18 ከመቶ የሚሆነው ደግሞ በግል የጤና ተቋማት የሕክምና አገልግሎቱን እንደሚያገኝ አንስተዋል፡፡

መንግስት ወደ ውጪ በመሄድ የሚገኘውን የሕክምና አገልግሎት ለማስቀረት የተለያዩ ሪፈራል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎችን እየገነባ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ጤና ሥርዓት በተደራሽነት፣ በባለሙያዎች አቅም ግንባታ፣ በሕክምና ግበዓቶች አቅርቦትና ፍትሃዊነትረገድ ጥሩ መሻሻል ማሳየቱን አውስተዋል፡፡

የኮሌራ በሽታ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መከሰቱን ጠቅሰው÷መንግስት በሽታውን ለመከላከል ክትባት ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የጤና ዘርፉ ዘመኑን የዋጀ አገልገሎት እንዲሰጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡም ሚኒስትሯ ጠይቀዋል፡፡

በአቤል ንዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.