Fana: At a Speed of Life!

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ማስተካከል ተችሏል – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢኮኖሚው ዘርፍ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ማስተካከል መቻሉን የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አዘጋጅነት በኢኮኖሚ ዘርፍ ከሕብረተሰቡ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለመተግበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ በመገባቱ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡

ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ በምርት አቅርቦት በኩል በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው÷በዚህም ይስተዋል የነበረውን የዋጋ ንረት መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በባንኮች እና በጥቁር ገበያ መካከል የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ልዩነት ለማስተካከል ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ተናግረዋል፡፡

የኑሮ ውድነቱ እንደየ ግለሰቡ ገቢ የተለያየ በመሆኑ ገቢያቸው እየጨመረ የመጣ የሕብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ውድነቱ ጫና ላያሳድርባቸው ይችላል ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው፤ በአንጻሩ ቋሚ ደመዎዝተኛው ላይ የኑሮ ውድነቱ አሁንም እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን ለማስተካከል የደመዎዝ ማሻሻያ መደረጉን አስታውሰው÷ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ አሁንም ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ስኬታማ መሆኑን የገለጹት ሚኒስተር ዴዔታው÷ ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እና በትብብር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በመንግስት በኩል ምንም አይነት የግብር ጭማሪ አለመደረጉን ጠቅሰው ÷ የማህበረሰቡን የኑሮ ጫና ለማቃለል መንግስት ለነዳጅ 70 ቢሊየን ብር በጀት በመመደብ ድጎማ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን ድሕነት ለመቀነስ የመንግስት እና የሕብረተሰቡ ርብርብ አስፈላጊ መሆኑንም ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.