Fana: At a Speed of Life!

ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው የቡና ምርት ወደ ውጭ ተልኳል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት 8 ወራት ብቻ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው የቡና ምርት ወደ ውጭ መላኩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 21ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።

ባለፉት ዓመታት በቡና ምርት ላይ የመጣውን እመርታ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያቸው÷ ቡና በለውጡ ማግስት 700 ሚሊየን ዶላር ገደማ በዓመት ኤክስፖርት ይደረግ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ባለፈው ዓመት የቡና ምርት ከፍተኛ ኤክስፖርት የተመዘገገበበት እንደሆነ አንስተዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት ከቡና ኤክስፖርት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ወጤት የተመዘገበበት ዓመት እንደሆነም አመላክተዋል።

ዘንድሮ ባለፉት 8 ወራት ብቻ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው የቡና ምርት ወደ ውጭ መላኩን ጠቅሰው፤ በሚቀጥሉት አራት ወራት በታቀደው ልክ ከተፈጸመ 2 ቢሊየን ዶላር ቡና ኤክስፖርት እናደርጋለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ እያደገ የመጣው የሕዝብ ቁጥርና የቡና ፍጆታ በሚመለከት ጥናት ሳይደረግ የተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ማወቅ ይቻላል በማለት ገልጸው÷ ይህም ቡና ላይ ስር ነቀል ለውጥ መምጣቱን የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

ቡናው ከሌላው ምርት ይልቅ በሀገር ውስጥ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው ምርት እንደሆነም አመልክተዋል።

በሻይ ምርት ላይም እየተሰራ ያለው ሥራ ተስፋ ሰጪ መሆኑን አንስተው፤ በገጠር አካባቢዎች በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.