ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛዋ ከፍተኛ የስንዴ አምራች ሀገር ሆናለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛዋ ከፍተኛ የስንዴ አምራች ሀገር ሆናለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት 8 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ስምንት ወራት የተገኘውን የኢኮኖሚ እቅድ አፈጻጸም በቀጣይ አራት ወራት አጠናክሮ ማስቀጠል ከተቻለ ከዕቅዱ በላይ ማሳካት እንደሚቻልም ነው የተናገሩት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው ባለፉት ስምንት ወራት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ውጤት ተመዝግቧል፡፡
ባለፉት አምስትና ስድስት አመታት በተከናወኑ ስራዎች ዘንድሮ ብቻ የአነስተኛ አርሶ አደሮች የሰብል ሽፋን ከ17 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር ወደ 20 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር ማደግ ችሏል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
እስካለፈው ዓመት ድረስ 8 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም የተሸፈነ ሲሆን፤ በዘንድሮው ዓመት ወደ 11 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር ማደግ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
በዘንድሮው የመኸር እርሻ 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በስንዴ መሸፈኑን ገልጸው፤ በበጋ መስኖ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መታረሱን አስረድተዋል፡፡
በጥቅሉ በዚህ ዓመት 7 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር በስንዴ ሰብል የተሸፈነ ሲሆን፤ ከዚህም ከ300 ሚሊየን ኩንታል ያላነሰ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስንዴ አምራች ሀገር በመሆን በአፍሪካ አንዷ መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ