ከ580 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት ከ580 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡
በምላሻቸውም በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስምንት ወራት ከ580 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ላይ እየሞከረች ያለችው ከጥቅል ሀገራዊ ምርት 7 በመቶ ገቢ ለማስገባት መሆኑን ጠቁመው÷የዘንድሮው ገቢ የሚበረታታ ቢሆንም፣ በቀጣይ መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ የእዳ ሽግሽግ ለማካሄድ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አንስተው÷በዚህም ኢትዮጵያ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገደማ የእዳ ሽግሽግ ማግኘቷን አንስተዋል፡፡
ባለፉት 8 ወራትም ከወጪ ንግድ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን ጠቁመው÷ይህም ከየትኛውም ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም ከነበራት የመጠባበቀያ በጀት አሁን ላይ ከእጥፍ በላይ መጠባበቂያ በጀት እንዳላትም አስረድተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ