በሚቀጥሉት 6 ወራት የሕዳሴ ግድብን ሪቫን እንቆርጣለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ሪቫን እንቆርጣለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡
በምላሻቸውም የሕዳሴ ግድብ በሁሉም ኢትዮያውያን ትብብር ያለምንም ብድር እየተከናወነ የሚገኝ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ሪቫን እንቆርጣለን ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡
ከግብጽ ወንድሞቻችን ጋር በውይይት ይበልጥ መደጋገፍ እንዳለብን እናምናለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በትብብር አብረን ብንሰራ የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ትስስር ማጠናከር ይቻላል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ከግብጽ ጋር አሁንም ለውይይት፣ ለድርድር እና የሕዳሴ ግድብ ያለበትን ሁኔታ ለማሳየት ዝግጁ መሆኗን አስገንዝበዋል፡፡
ሕዳሴ የአፍሪካ ኩራት ነው፤ ለመላው አፍሪካ መቻል ያሳየንበት ነው፤ ስህተትን ያረምንበት ነው፤ 74 ቢሊየን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ የያዝንበትም ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ግድቡ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጭምር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመው÷ ግድቡ በመሞላቱ ምክንያት አስዋን ግድብ ላይ የጎደለ ውሃ የለም፤ እኛም ቃል የገባነው ይህ እንዲፈጸም ነበር፤ ይህም በተግባር ተሳክቷል ነው ያሉት።
በመላኩ ገድፍ