የግጭት ተፈጥሮና ዕድገት ከመሰረቱ የማየት ልምምድ ካልፈጠርንና ላይ ላዩን የምናይ ከሆነ እንስታለን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግጭት ተፈጥሮ እና ዕድገት ከመሰረቱ የማየት ልምምድ ካልፈጠርንና ላይ ላዩን የምናይ ከሆነ እንስታለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም÷ ግጭት ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር እኩል የተፈጠረ ነው ብለዋል።
መንግሥት ሰላምን ያስቀደመ፣ ሰላምን በይፋ የሚናገርና የሚተጋ መሆን እንዳለበት ጠቁመው÷ መንግስት በብቸኝነት ኃይል የመጠቀም ሥልጣን ያለው አካል መሆኑንም አንስተዋል።
መንግስት የሚዋጋው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ለዘላቂ ሰላም ሊጋጭ እንደሚችልም አስገንዝበዋል።
በህዝብ የተመረጠውን መንግስት በኃይል ለማፍረስ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተራ ልምምድ ሆኗል በማለት ገልጸው÷ በኃይል ሥልጣን መያዝን አቅልሎ የማየት ችግር በስፋት እንዳለም ጠቁመዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት ከአንድም ጎረቤት ጋር ያልተዋጋነው የሚያጋጩ ነገሮች ስለሌሉ ሳይሆን ግጭት ጉዳት አምጪ እንደሆነ ስለምናውቅ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በየመድረኩ ሰላም ሰለም የምንለው ሰላምን ስለምንፈልግ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ከማንኛውም አካል ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በሰላምና በድርድር ግጭቶችን ለመፍታት መንግስት ሁሌም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በአድማሱ አራጋው