Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ፓኪስታን የፓርላማ ዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የፓርላማ ዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እና ልዩ መልዕክተኛ ጀማል በከር (ዶ/ር) ከፓኪስታን የሴኔት ሊቀመንበር ሲዬድ ዩሱፍ ራዛ ጊላኒ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ሀገራቱ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ አቪዬሽን፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሰላምና ፀጥታን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ትብብራቸውን ለማጎልበት እንዲሁም የፓርላማ ዲፕሎማሲ ወዳጅነታቸውን ለማጠናከር ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል።

ሁለቱ ወገኖች በተለይም የከፍተኛ ደረጃ ልዑካን ቡድኖች ልውውጥ እና በፓኪስታን ሴኔት የኢትዮጵያ-ፓኪስታን የፓርላማ ወዳጅነት ቡድን በማቋቋም ግንኙነቶችን ለማጠናከር መክረዋል።

አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለክልላዊ ውህደት የወሰደቻቸውን ተነሳሽነቶች እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበር የሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎችን ለመዋጋት ያለመ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነትን በማስፈን ረገድ የምትጫወተውን ሚና በተመለከተ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በተደረገው በኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ምክንያት የተፈጠሩትን ልዩ የንግድ እና የኢንቨስትመንት እድሎችን አብራርተዋል።

የፓኪስታን የሴኔት ሊቀመንበር ሲዬድ ዩሱፍ ራዛ ጊላኒ በበኩላቸው ፓኪስታን ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታ እንደምትሰጥ ጠቅሰው፤ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ትብብሯን ለማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ፈጣን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትን በማረጋገጥ ልዩ አመራር ላሳዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸውን በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.