አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮምቦልቻ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የኮምቦልቻ አውሮፕላን ማረፊያን የአገልግሎት አሰጣጥ እና የማስፋፊያ ግንባታ ሂደት ጎብኝቷል።
የጎብኝ ቡድኑ መሪ ዘውዱ ታደሰ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ተቋሙ በውስን ቦታ ሳይገደብ በርካታ ቁጥር ላላቸው ደንበኞች እየሰጠ ያለውን አገልግሎት በጥንካሬ አንስተዋል።
ለደኅንነት እና ሌሎች መሰል ጥያቄዎች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበው፤ የማስፋፊያ የግንባታ ሂደቱን በተመለከተ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ መሥራት ያስፈልጋል ለዚህም ቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ ያደርጋል፡፡
የማስፋፊያ ሥራው ተጓትቶ እንደነበር አውስተው፤ አሁን ያለው የግንባታ ሂደት አበረታች ነው ማለታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
በማስፋፊያው መሠረታዊ የግንባታ ሂደቶች እና ከኤሌክትሪክ ጋር የተያያዙ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡
አካባቢው የኢንዱስትሪ ማዕከል እንደመሆኑ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።