በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉ 65 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አካባቢ በመሆን በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ነበሩ የተባሉ 65 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተቋሙ አስታውቋል፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ በተጨማሪም በአጠቃላይ ሰባት በሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ተሰማርተዋል የተባሉ ቤቶች መታሸጋቸውን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በተለያየ የሕገ-ወጥ የድለላ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ፣ የሥራ ከባቢውን በማወክ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር እየፈጠሩ ያሉ፣ በተለያየ የማጭበርበር እና የማታለል ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩ እና በሕገ-ወጥ መንገድ የኦን ላይን የአስቸኳይ ፓስፖርት የሚሞሉ መሆናቸውን ተገልጿል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት፤ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 አሥተዳደር በቅንጅት ባደረጉት ልዩ ኦፕሬሽን መሆኑ ተገልጿል፡፡