Fana: At a Speed of Life!

ቱርክ የሩሲያና ዩክሬንን የሰላም ጥረት እንድታግዝ በአሜሪካ ጥሪ ቀረበላት

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቱርክ ሩሲያ እና ዩክሬንን ለማሸማገል የሚደረገውን ጥረት እንድታግዝ አሜሪካ ጥሪ አቅርባለች፡፡

በአሜሪካ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን ከአሜሪካ አቻቸው ማርኮ ሩቢዮ ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብሮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

ሁለቱ ሚኒስትሮች በነበራቸው ውይይት ሩሲያ እና ዩክሬን የተኩስ አቁም በማድረግ ወደ ሰላም ስምምነት በሚመጡበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ምክክር አድርገዋል።

በዚህ ወቅት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር÷ አንካራ ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ከሩሲያ እና ዩክሬን እንዲሁም ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገራት ጋር ጠንካራ የንግድ ግንኙነት እደነበራት አስታውሰዋል፡፡

ቱርክ በ2022 ሁለቱን ሀገራት ለማሸማገል የተካሄደውን ስብሰባ ማስተናገደን ጨምሮ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጥረት ስታደርግ እንደነበር አስታወሰው፤ አሁንም ሀገራቱ ወደ ሰላም እንዲመጡ የሚደረገውን ጥረት እንድታግዝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ዘመን በአንካራ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንደሚነሱ ተስፋቸውን የገለፁት ሩቢዮ÷ ይህም ቱርክ እና አሜሪካ ወደ ቀደም የሁለትዮሽ ትብብራቸው የሚመለሱበትን እድል እንደሚፈጥር ገልፀዋል፡፡

ሀካን ፊዳን በበኩላቸው÷ በመካከለኛው ምስራቅ ሰላምን ለማስፈን በጋዛ ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.