Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ እና ኮሚሽኑ በትብብር በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ላይ መከሩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፍትሕ ሚኒስቴር እና የኢትየጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቀጣይ በጋራ በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ላይም፤ በሽግግር ፍትሕ ትግበራ ሂደት፣ በሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሀገራዊ ሪፖርት ዝግጅት እና ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ቀርበው ምክክር ተደርጓል፡፡

ተቋማቸው የሰብዓዊ መብትን በተመለከተ ከሚሠራቸው ተግባራት መካከል፤ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ-ግብር መከታተል፣ የታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ክትትል፣ ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ የንቃተ ሕግ ሥራዎች መሥራት እና ሌሎች ተግባራት እንደሚገኙበት የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርአያሥላሴ አብራርተዋል፡፡

በቀጣይ ከሽግግር ፍትሕ የትግበራ ሂደት፣ ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ዝግጅት፣ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እና በሌሎች ከሰብዓዊ መብት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሥራዎችን ከኮሚሽኑ ጋር በቅንጅት በመሥራት ውጤታማ በሆነ መልኩ መተግበር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትየጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብት ተግባራትን በተመለከተ ከሚኒስቴሩ ጋር እያደረጋቸው ያሉ ውይይቶች ተስፋ ሰጭ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በቀጣይ በሚኖሩ ተግባራት ቴክኒካል ቡድን በማዋቀር ጭምር ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ በትብብር እንደሚሠሩ ማረጋገጣቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.