Fana: At a Speed of Life!

ከ1 ሺህ ወራት ኢባዳ የላቀ ምንዳዋ ሚዛን የሚደፋው “ለይለቱል ቀድር”

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በረመዷን ወር ከ1 ሺህ ወራት ወይም ከ83 ዓመት ከ3 ወራት ኢባዳ በላይ የላቀ ምንዳ ያላት አንድ ሌሊት “ለይለቱል ቀድር” ትገኛለች፡፡

ይችን በረከተ ብዙ “ለይለቱል ቀድር” ምዕመኑ በንቃት እንዲጠብቃት አስተምኅሮቱ ያዛል፡፡

“ረመዷን” ማለት . . .

በቁርአን ላይ እንደተገለጸው፥ ከአላህ ዘንድ የወራት ቁጥር 12 ናቸው። እነሱም፦ ሙሀረም፣ ሰፈር፣ ረቢዕ አልአወል፣ ረቢዕ አልሳኒ፣ ጅማድ አልኡላ፣ ጅማድ አልአኺራ፣ ረጀብ፣ ሻዕባን፣ ረመዷን፣ ሸዋል፣ ዙል ቀኢዳ እና ዙል ሂጃ ናቸው።

ከላይ በቀረበው አገላለጽ መሰረት፥ “ረመዷን” ማለት ከ12ቱ ወራት የዘጠነኛው ሥያሜ ነው።

“ረመዷን” ከሌሎቹ ወራት በምን ይለያል?

ረመዷን ከሌሎች ወራት የሚለይበት በርካታ ምክንያት እንዳሉት ይገለጻል።

ከሌሎች ወራት ከሚለይባቸው ምክንያቶች አንዱ “ቁርአን የወረደበት ወር መሆኑ ነው” ይላሉ የእስልምና ሐይማኖት አስተማሪዎች፤ ይህም በቁርአን ላይ ስለመጠቀሱ በማረጋገጥ።

በተጨማሪም ረመዷን የሠደቃ፣ የራህመት፣ የጀነት በር የሚከፈትበት፣ የጀሃነም በር የሚዘጋበት፣ በጎ ሥራዎች ሲሠሩ ከአላህ ዘንድ እጥፍ ክፍያ (አጅር) የሚያስገኝ በመሆኑ ከሌሎች ወራት እንደሚለይ ያብራራሉ።

እንዲሁም ረመዳን “ለይለቱል ቀድር” የተሰኘች የ1ሺህ ወራት የአምልኮ ምንዳ ልታስገኝ የምትችል አንዲት ሌሊት የምትገኝበት ወር በመሆኑ ልዩ ነው ይላሉ።

ስለ “ረመዷን” ጾም አላህ ምን አለ?

የበረከት ማግኛ ወር በመሆኑ ሙስሊሞች እንዲጾሙ ይጠበቃል ይላሉ መምህራኑ።

ይህንም “እናንተ ምዕመናን ሆይ በእናንተ ላይ ጾምን እንድትጾሙ ግዴታ ተደርጎባችኋል፤ ከእናንተ በፊት በነበሩት ምዕመናን ላይ ግዴታ እንደተደረገው ሁሉ በእናንተም ላይ ግዴታ ተደርጓል” ብሎ አላህ በቁርአን ላይ ተናግሯል ይላሉ።

በሌላ በኩል “ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው ካለ ወይም በጉዞ ላይ ከሆነ መጾም ስለማይችል ጾሙን ይተው እና በሌላ ጊዜ ያልጾመውን ያህል ቀን ቆጥሮ ‘ቀዷ’ (እዳውን) እንዲከፍል አዝዣለሁ” ሲል አላህ በቁርአን የተናገረውን በዋቢነት ያነሳሉ።

ይህን መፈፀም እንደሚጠበቅም ያስገነዝባሉ።

“እናንተን ሊያግራራላችሁ ነው እንጂ አላህ የሚፈልገው ሊያስጨንቃችሁ አይፈልግም” ብሎ በተናገረው መሰረት በወቅቱ መጾም ላልቻሉ አማራጭ መቀመጡን ነው መምህራኑ የሚያስረዱት።

የ “ረመዷን” ትሩፋት!

የረመዷን ወር በርካታ ትሩፋት እንዳሉትም ነው መምህራኑ የሚያመላክቱት፡፡

ቁርአን በብዛት የሚቀራበት፣ “ቀልቦች” ወደ ፈጣሪያቸው ቀጥ የሚሉበት፣ ርኅራሔ የሚበዛበት፣ ሠደቃ የሚሠደቅበት፣ የቸርነት፣ የልገሣ፣ የደግነት፣ የተካፍሎ መብላት እና የእንረዳዳ ወር መሆኑ ከትሩፋቶቹ መካከል እንደሚጠቀሱ ያብራራሉ።

የ “ረመዷን” የመጨረሻ ሣምንት!

የረመዷን ወር በሦት አሥር ቀናት የሚከፈል ሲሆን፥ ከሦስቱ አሥሮች የመጨረሻው አሥር (“አሸረ አልአዋኺር”) ይሰኛል።

እንደ መምህራኑ ገለፃ፥ በአጠቃላይ “ረመዷን” የ “ኢባዳ” ወር ቢሆንም የሦስተኛው አሥር ቀናት የተለዩ በጾም በጸሎት ማሳለፊያ ጊዜ (የ”ኢባዳ” ሌሊቶች) ናቸው።

የረመዷን የመጨረሻው ሣምንት ሌሊቶች ከሌሎች ሣምንታት የሚለዩበት ምክንያት እንዳለም ይገልጻሉ።

ከምክንያቶቹ መካከል፥ ነብዩ መሐመድ (ሰለሏህ ዓለይሂ ወሰለም) ያደርጉት እንደነበረው “ሥራ ትቶ፣ እራስን አቅቦ ለ”ኢባዳ” ማስቀመጥ ቀኑንም ሌሊቱን በመስጂድ ማሳለፍ (“ኢህቲካፍ” መግባት) አንዱ ነው” ይላሉ።

በመሆኑም ወደ መስጂድ ለ “ኢህቲካፍ” የገባ ምዕመን ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ካላጋጠመው በስተቀር ከመስጂድ መውጣት የማይቻልበት ሣምንት መሆኑንም ነው የሚጠቅሱት።

ሌላኛው ምክንያት በእነዚህ ሌሊቶች፥ የተራዊህ እና የተሃጁድ ሶላት ይሠገዳል፣ ሌሊቶቹ ያለዕንቅልፍ ቁርአን በመቅራት እንዲያልፉ ይደረጋል፣ መሻይኾች፣ ዑለማዎችና የመስጂድ አሰጋጆች በተለያየ የሶላት ወቅት ላይ (በዙህር፣ ዓስር፣ መግሪብ፣ ኢሻ)፣ በማኅበራዊ ጉዳይ፣ በሥነ ምግባር፣ በአምልኮ እንዲሁም በእምነቱ ዘሪያ (በዓቂዳ ጉዳይ ላይ) ምክር ይሰጣሉ ነው ያሉት።

ሙስሊሞች “ረመዷን” ን ለቀጣዮቹ 11 ወራት የባሕርይ፣ የሥነ ምግባር፣ የአምልኮ የጥንካሬ እና የብቃት አቅም የሚያጎለብቱበት ልዩ ወር እንደሆነም ይነሳል፡፡

የመጨረሻው ሣምንት ሌሊቶችንም በንቃት በኢባዳ እንደሚያሳልፏቸው ነው የሚገልጹት፡፡

በዚሁ የረመዷን የመጨረሻ ሣምንት የጾም ወቅት በኢትዮጵያ በበርካታ መስጂዶች የተሃጁድ ሶላት እንደሚሠገድም ይጠቁማሉ፡፡

በተጨማሪም ረጅም ሩኩዕ፣ ረጅም ስጁድ፣ ረጂም ቂያም ያካተተ ሶላት ይሠገዳል ነው የሚሉት፡፡

በአጠቃላይ ይህ ሁሉ ለኢባዳ የሚደረገውን መስዋዕትነት በአላህ እንደመገዛት የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለማሰልጠን ጭምር መሆኑን ያነሳሉ።

ከ1 ሺህ ወራት ኢባዳ የላቀ ምንዳ ያላት አንድ ሌሊት (ለይለቱል ቀድር)

ከቅዱሱ የረመዷን ወር የመጨረሻ ሣምንት ውስጥ ‹‹ለይለቱል ቀድር›› የምትባል በረከቷ የበዛ ሌሊት አለች፡፡ ይችኑ ሌሊት ‹‹ኸይሩን ሚን አልፊሸህር›› ብሏታል ቁርአን፡፡

እንደ መምህራኑ ገለጻም፤ “በእዚች ሌሊት ላይ ጠንክሮ ማምለክ የ1 ሺህ ወር ወይም (83 ከ3 ወራት በላይ) አላህን የመገዛት ያህል ይቆጠራል”፡፡

ሙስሊሞች ይችን በረከተ ብዙ ሌሊት በኢበዳ ለማሳለፍ በንቃት መጠበቅ እንደሚገባቸውም መክረዋል፡፡

‹‹ከአሥሩ ቀናት መካከል የትኛዋ ነች›› ተብለው ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ተጠይቀው እንደነበር ያነሱት መምህራኑ፤ ነብዩም ሲመልሱ ‹‹ተነግሮኝ ልነግራችሁ ስመጣ እረሳሁት›› እንዳሉ ይናገራሉ፡፡

ለምንድን ነው አላህ ያስረሳቸው? ለሚለው ጥያቄ ‹‹ያቺ ቀን ከተነገረች ሙስሊሞች ያቺን ቀን ብቻ ኢባዳ አድርገው ሌሎቹን ቀናት ችላ እንዳይሏቸው ነው። አሥሩንም ቀናት በትጋት ኢባዳ እንዲያደርጉ ታስቦ ነው›› ብለዋል ነብዩ፡፡

እና እንዴት እናድርግ ሲሏቸውም ” ለማንኛውም በጎደሎ ቁጥር ፈልጓት” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን መምህራኑ ያወሳሉ፡፡ ጎደሎ ቁጥር ማለትም፥ “21ኛው፣ 23ኛው፣ 25ኛው፣ 27ኛው እና 29ኛው ሌሊቶች ናቸው። ነብዩ ቁርጥ አድርገው ሳይናገሩ ከእነዚህ መካከል ፈልጓት ነው ያሉት።

የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ባለቤት አይሻ ነብዩን “ለይለቱል ቀድር” ሲያጋጥመኝ ምንድን ነው ማለት ያለብኝ ብለው ጠይቀዋቸው ነብዩ ሲመልሱ “ጌታዬ አንተ ይቅርታን ትወዳለህና ይቅር በለኝ” ብለሽ ሌሊቱን ሙሉ ዱዓ አድርጊ ብለው እንደመከሯቸውም ይገለጻል፡፡

ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አሥሩንም ሌሊቶች እንቅልፍ ያለባቸውን ቤተሰቦቻቸውን ቀስቅሰው የጋራ ኢባዳ እና የጋራ አምልኮ (በጀመዓ መጸለይ) በማድግ ሳይተኙ ያሳልፉ ነበር የሚሉት መምህራኑ፤ እኛም እሳቸውን የምንከተል በመሆናችን ‹‹በአላህ መልዕክተኛ መልካም አርአያ አላቸው፤ እሳቸው የሚሉትን ሥሩ›› ስለተባልን ኢባዳችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

ሌሊቱ በዱዓ፣ በጸሎት፣ እንዲያልፍ አላህ ይቅር እንዲል ሙስሊሞች የሚማፀኑበት ሌሊት መሆኑም ተመላክቷል።

ረመዷን ሠደቃ የሚሰጥበት፣ አቅመደካሞች የሚረዱበት፣ የመተጋገዝ ወር እና ለማፍጠሪያ ማዕድ ማጋሪያ ጊዜ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.