Fana: At a Speed of Life!

ፊቼ ጫምባላላ የወል ትርክትን ለመገንባት የሚኖረው ሚና ጉልህ ነው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፊቼ ጫምባላላ የእርቅ፣ የሰላም፣ የአብሮነት እና የወንድማማችነት እሴቶች ከማጎልበቱ ባሻገር ለሀገር ግንባታና የወል ትርክትን ለመገንባት የሚኖረው ሚና ጉልህ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለፊቼ ጫምባላላ የዘመን መለወጫ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

የፊቼ ጫምባላላ የዘመን መለወጫ በዓል የሲዳማን ሕዝብ ማንነትና ባህል ከማስተዋወቅ ባለፈ የክልሉን የቱሪዝም ልማትና ዕድገት በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም አመላክቷል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

እንኳን ለፊቼ ጫምባላላ የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል ተመዝግቦ የሚገኘው የፊቼ ጫምባላላ የዘመን መለወጫ በዓል የሀገር ሀብትና ቅርስ መካከል አንዱ ነው።

በዓሉ ዘንድሮ በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ከተማ መጋቢት 18 በሲዳማ ባህል አዳራሽ እንዲሁም መጋቢት 19/2017 ዓ/ም በሶሬሳ ጉዱማሌ በተለያዩ ትዕይንቶች ታጅቦ በድምቀት ይከበራል፡፡

ፊቼ ጫምባላላ በሲዳማ ሕዝብ ዘንድ የአዲስ ዘመን መለወጫና ማብሰሪያ ሆኖ የሚከበር ታላቅ በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል በኅብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ ባህላዊ ትውፊት ነው፡፡

ፊቼ ጫምባላላ የአብሮነት፣ የሰላም፣ የፍቅርና የመረዳዳት እሴቶች ጎልቶ የሚታዩበትም ነው፡፡ በዓሉ የሲዳማ ሕዝብ ዘመን መለወጫ በዓል ብቻም ሳይሆን የነበረ ቂምና ቁርሾ ተወግዶ ይቅርታ የሚሰፍንበት የእርቅና የሰላም ባህላዊ ትውፊት ነው። በመሆኑም ፊቼ ጫምባላላ የሰላም፣ የእርቅና የይቅርታ ተምሳሌት የሆነ ቅርሳችን ነው፡፡

የሲዳማ ሕዝብ የራሱ የሆነ የቀን አቆጣጠር ያለው ሲሆን ቀናትን፣ ሳምንታንና ወራትን በራሱ ባህላዊ የአቆጣጠር ዘዴ ተከትሎ ይጠቀማል፡፡ በበዓሉ ከሰው እስከ እንስሳት እንዲሁም ለዕፅዋትና አራዊቶች መልካም ምኞት የሚንጸባረቅበት ትውፊት ነው፡፡ በመሆኑም በዓሉ የቀደምት አባቶችን የዕውቀት ከፍታ ማሳያ፣ የሕዝቡን የጥበብ ጥግ ታሪክ ባለቤትነት መገለጫም ጭምር ነው፡፡

በዓሉ የሲዳማን ሕዝብ ማንነትና ባህል ከማስተዋወቅ ባለፈም የክልሉን የቱሪዝም ልማትና ዕድገት በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም ፊቼ ጫምባላላን የእርቅ፣ የሰላም፣ የአብሮነት እና የወንድማማችነት እሴቶች ከማጎልበቱም ባሻገር ለሀገር ግንባታና የወል ትርክትን ለመገንባት የሚኖረው ሚና ጉልህ ነው፡፡

ስለሆነም መልካም ታሪካዊና ባህላዊ እሴቱን አስጠብቆ ቀጣዩ ትውልድ እንዲሸጋገር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡

እንኳን ለፊቼ ጫምባላላ አደረሳችሁ!
Ayidde Cambalaalla!
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.