ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከቻይና ብሔራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋር በትብብር ለመስራት ተስማማ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከቻይና ብሔራዊ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጋር በትብብር ለመስራት ስምምነት አድርጓል።
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አድማሱ ዳምጠው በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የባህል ዘርፍ አማካሪ ዣንግ ያዌይን እና በቻይና ኢኮኖሚያዊ እና ቴክኒካል ትብብር የዓለም አቀፍ ልውውጥ መምሪያ ምክትል ዳይሬክተር ፌንግ ቦ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በስምንት የሀገር ውስጥ እና በሁለት የውጭ ቋንቋዎች በቴሌቪዥን፣ በራዲዮ እና በዲጂታል የሚዲያ አማራጮች ተደራሽ መሆኑን አቶ አድማሱ ገልጸዋል።
ከቻይና ብሔራዊ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ጋር በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመስራት ስምምነት መደረጉን ጠቁመው፤ ተቋሙ በተለያዩ ዘርፎች ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዚህም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ፣ የጥበብ፣ የፈጠራ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ዝግጅቶችን ለማቅረብ እና በጋራ ለመስራት ስምምነት መደረጉን አብራርተዋል።
በተጨማሪም የአቅም ግምባታ፣ የቴክኖሎጂ ድጋፍ፣ የልምድ ልውውጥ እና ስልጠናዎችን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን በሚያደርጉባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን እና መስማማታቸውን ተናግረዋል።
በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የባህል ዘርፍ አማካሪ ዣንግ ያዌይ በበኩላቸው ሀገራቸው በዘርፉ የተለያዩ ጠንካራ ፕሮጀችቶች እንዳላት ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር የመስራት ፍላጎት እንዳለ ገልጸዋል።
አክለውም የባህል፣ የስልጠና እና የልምድ ልውውጥ ዙሪያ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
ፌንግ ቦ በተለያዩ የዓለም ሀገራት ተወዳጅነትን ያተረፉ የቻይና ፕሮግራሞችን ለአፍሪካ ሀገራት በመስጠት የባህል እና የቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች እንደሚሰሩ ጠቁመው፤ በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በኩል የተለያዩ ዝግጅቶችን የማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው አብራርተዋል።
በዮናስ ጌትነት